Uncategorized

የኦጋዴን የነዳጅ ይዞታዎች ለቻይና ኩባንያ ተሰጡ

(ሪፖርተር)በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በኦጋዴን ቤዚን ውስጥ የሚገኙ የማሌዥያ ኩባንያ በሆነው ፔትሮናስ ተይዘው የቆዩ የካሉብና የሂላላ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችትና ሌሎች ስምንት የነዳጅ ፍለጋ ቦታዎች፣ ፔትሮትራንስ ለተባለ ተቀማጭነቱ በሆንግ ኮንግ ለሆነ የቻይና ኩባንያ ተሰጡ፡፡

የማዕድን ሚኒስቴርና ፔትሮትራንስ የፔትሮሊየም ልማት የነዳጅ ፍለጋና የምርት ክፍፍል ስምምነቶችን ሐምሌ 17/2003 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ የፈረሙት የማዕድን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉና የፔትሮትራንስ ሊቀመንበር ሚስተር ጆን ቺን ናቸው፡፡

ስምምነቱ ፔትሮትራንስ በካሉብና በሂላላ የሚገኘውን አራት ትሪሊዮን ሜትር ኪዩብ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምች ለማልማት የሚያስችል ሲሆን፣ ብሎክ 3 እና 4፣ 11 እና 15፣ 12 እና 16፣ 17 እና 20 በተባሉት ቦታዎች የተፈጥሮ ዘይትና የጋዝ ፍለጋ ሥራ እንዲያካሂድ ይፈቅዳል፡፡ በተጨማሪም በገናሌ አካባቢ 0.7 ትሪሊዮን ኪዮቢክ ጫማ መጠን ያለው ፔትሮናስ በቆፈረው የፍለጋ ጉድጓድ የተገኘው የጋዝ ክምችት ለፔትሮትራንስ ከተሰጡት የነዳጅ ይዞታዎች ውስጥ ተካቷል፡፡ ከጋምቤላ በቀር ሌሎቹን የፔትሮናስ የነዳጅ ይዞታዎች በሙሉ ለቻይናው ኩባንያ ተሰጥቷል፡፡

ፔትሮናስ በኢትዮጵያ የነበሩትን የነዳጅ ፍለጋና የልማት ሥራዎች አቋርጦ ከወጣ በኋላ፣ የማዕድን ሚኒስቴር ሰባት የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን መርጦ በፔትሮናስ ተይዘው የነበሩ በኦጋዴን የሚገኙ የነዳጅ ይዞታዎችን በጨረታ እንዲወስዱ ባለፈው የካቲት ወር ጋብዟል፡፡

ይህንን ተከትሎ ሰባቱም ኩባንያዎች የጨረታውን ሰነድ የገዙ ሲሆን፣ ከሰባቱ አራት ኩባንያዎች (ፔትሮትራንስ፣ የሼክ መሐመድ ሑሴን አሊ አላሙዲ ኩባንያ የሆነው ኖክ፣ ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ የተባለ ኢትዮጵያ የነዳጅ ኩባንያና ኮብለማር የተባለ የሲሼልስ ኩባንያ) ዕቅዳቸውን ለሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ አቅርበዋል፡፡

“እቅዳቸውን ካቀረቡት አራት ኩባንያዎች ፔትሮትራንስ ያቀረበው ከሁሉም ይበልጣል፤” ብለዋል ወ/ሮ ስንቅነሽ፡፡ “መንግሥት የሚፈልገው የተፈጥሮ ጋዙን በፍጥነት ወደልማት ማስገባት ነው፡፡ ትኩረት የሰጠነው ለክፍያው ሳይሆን የነዳጅ ልማት ዕቅድ ላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የቻይናው ፔትሮትራንስ ያቀረበው የኢንቨስትመንት ዕቅድ ሌሎቹ ካቀረቡት ጋር አይገናኝም፤” ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡ ፔትሮትራንስ ለመንግሥት 130 ሚሊዮን ዶላር በመጪው 10 ዓመት የሚከፍል ሲሆን፣ ይህም የካሉብና የሂላላ የጋዝ ክምችትን ለማግኘትና ከተገኘም በኋላ ለተሠሩ የተለያዩ ሥራዎች ወጪ ማካካሻ ነው፡፡ ኩባንያው ለተዋዋለባቸው አራት የነዳጅ ፍለጋና የምርት ክፍፍል ስምምነቶች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊዮን ዶላር የፊርማ ጉርሻ ይከፍላል፡፡

ኩባንያው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱን በማውጣት በሚገነባው የጋዝ ማጣርያ አማካኝነት ጋዙን ወደ ፈሳሽ ነዳጅ በመቀየር ለዚሁ ተብለው በተሠሩ መርከቦች ኤክስፖርት እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ ጋዝ ኩባንያው በዘረጋው የማስተላፊያ ቱቦ ጂቡቲ ወደብ ድረስ ተጓጉዞ በከፍተኛ ቅዝቃዜና የግፊት ልዩነት በመፍጠር (Pressure Difference) ወደ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (Liquefied Natural Gas) ይለወጣል፡፡ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዙ ለዚሁ ተብለው በተሠሩ መርከቦች ለዓለም አቀፍ ገበያ ይቀርባል፡፡

ኩባንያው ባጠቃላይ ከ2.5 እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ መዋዕለ ነዋይ ያፈሳል፡፡ የተለያዩ የከርሰ ምድር ጥናቶችና (ሴይስሚክ፣ ግራቪቲና ማግኔቲክ ሰርቬይ) በማካሄድ የተለያዩ የተፈጥሮ ዘይትና የጋዝ ፍለጋ ጉድጓዶችን ይቆፍራል፡፡

የኩባንያው ሊቀመንበር ሚ/ር ቺን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጋዝ ማጣርያው ግንባታና የባንቧው ዝርጋታ ሥራ በአስቸኳይ ተጀምሮ በ30 ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ “እኛ በቻድ፣ በናይጄሪያና በሱዳን ነዳጅ አውጥተናል፡፡ በሱዳን 600 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ በ10 ወር ጊዜ ውስጥ ዘርግተናል፡፡ በቻይና 8,300 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ቧንቧ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጨርሰናል፡፡ በሱዳን፣ በቻድና በናይጄርያ ውጤታማ ሥራ ሠርተናል፣ ያንን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደግማለን፤” ብለዋል፡፡

ፔትሮትራንስ በኢትዮጵያ ለሚያካሂደው ሥራ ታዋቂ የሆኑ እንደነ ሳይኖፔክና ሲኤንፒሲ የተባሉ የቻይና ኩባንያዎችን በኮንትራት ይቀጥራል፡፡ ፔትሮትራንስ እ.ኤ.አ. በ1997 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ አፍሪካ ውስጥ በ15 አገሮች ይሠራል፡፡ በካዛክስታንና በኢንዶኔዢያም በነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ ተሰማርቷል፡፡

የካሉብ የተፈጥሮ ጋር ክምችት እ.ኤ.አ. በ1972 ዓ.ም. የተገኘ ሲሆን፣ የተለያዩ የውጪ ኩባንያዎች ማለትም የቀድሞው ሶቪዬት ሕብረት ኩባንያ ስፒ፣ የቻይናው ዜፕና ፔትሮናስን ጨምሮ በካሉብና በሂላላ አካባቢ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የጋዝ መሬቶቹን ወደግል ይዞታ ለማዛወር በተለያዩ ጊዜያት ያደረጋቸው ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡

ሴኮር የሚባል የአሜሪካ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ2001 የጋዝ ክምችቶችን ለማልማት የመግባቢያ ሰነድ ከፈረመ በኋላ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በ2001 ዓ.ም. ሜታኖል ጆይንት ስቶክና ስትሮይ ትራንስ ጋዝ የተባሉ የሩሲያ ኩባንያዎች የመግባቢያ ሰነድ ከፈረሙ በኋላ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ “የኢትዮጵያ መንግሥት ያምጣ እኛ ቴክኖሎጂውን እናቀርባለን፤” በማለታቸው ሳይካካ ቀርቷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2003 የፔትሮሊየም ምርት ስምምነት የተፈራረመው ሳይቴክ ኢንተርናሽናል የተባለ የዮርዳኖስ ኩባንያ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማምጣት ባለመቻሉ ስምምነቱ ተሰርዟል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2007 ውስጥ 80 ሚሊዮን ዶላር ከፍሎ የጋዝ መሬቶችን የተረከበው ፔትሮናስ ነበር፡፡ ፔትሮትራንስ አሁን ፔትሮናስ ካቀረበው የጋዝ ልማት ዕቅድ ጋር ተመሳሳይ ፕሮግራም አቅርቦ፣ ለፕሮጀክቱም 1.9 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አደርጋለሁ ብሎ ነበር፡፡ በእርግጥ በነዳጅ ፍለጋው መስክ ብዙ ሥራዎች የሠራ ቢሆንም፣ የጋዝ ማጣርያውን ሳይገነባና ቧንቧውን ሳይዘረጋ ጓዙን ጠቅለሎ ወጥቷል፡፡

ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥረቶች መጨረሻቸው ሳያምር በመቅረቱ አሁንስ ይሳካ ይሆን የሚል ጥርጣሬ በተለያዩ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ ይጉላላል፡፡ “አሁን ትክክለኛው ጊዜ የመጣ ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔር ይርዳን ብለዋል፤” ሚኒስትሯ ወ/ሮ ስንቅነሽ፡፡ ሚ/ር ቺን በበኩላቸው፣ ኩባንያቸው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ዘይት አግኝቶ ለማልማት ከፍተኛ ቁርጠኝነት ይዞ የመጣ ነው ብለዋል፡፡

በቃለየሱስ በቀለ

Advertisements

What do you say about this? እርስዎ ምን ይላሉ?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s