Uncategorized

ሄኒከን በሐረርና በደሌ ቢራ ፋብሪካዎች ላይ 100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ሊያደርግ ነው

የሐረርና የበደሌ ቢራ ፋብሪካዎችን በቅርቡ የገዛው ታዋቂው የሆላንድ ቢራ ጠማቂ ኩባንያ የሆነው ሄኒከን፣ ሁለቱን ቢራ ፋብሪካዎች ለማስፋፋትና አቅማቸውን ለማሳደግ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት 100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡

የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሄኒከን በሐረርና በበደሌ ቢራ ፋብሪካዎች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ መጠነ ሰፊ የሆነ የማስፋፊያ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ‹‹ፋብሪካዎቹን ሄኒከን በመግዛቱ በጣም ደስተኞች ነን፤ ምክንያቱም በቢራ ኢንዱስትሪ ውስጥ ቀዳሚ ከሆኑት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አንዱ በመሆኑ፣ ወደ ኢትዮጵያ በሚያመጣው የውጭ ኢንቨስትመንትና የካበተ ልምድ ባለቤት መሆኑን በማሰብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የፋብሪካዎቹ የሽያጭ ውል ባለፈው ረቡዕ በአቶ በየነና የሄኒከን የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ፕሬዚዳንት ሚስተር ቶም ዲማን በባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ የተፈረመ ሲሆን፣ ሐሙስ ምሽት ላይ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የሄኒከን ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ጆሃን ዶየር ኩባንያው በሐረርና በበደሌ ቢራዎች ላይ የስም ለውጥ እንደማያደርግ ገልጸው፣ የፋብሪካዎቹ የማምረት አቅም በ100 ፐርሰንት እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ፋብሪካዎቹ የሄኒከንን ቢራ እንደሚያመርቱና ኩባንያው አዲስ የቢራና የብቅል ፋብሪካ ሊገነባ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ሄኒከን የሐረር ቢራ ፋብሪካን በ78 ሚሊዮን ዶላር፣ የበደሌን ቢራ ፋብሪካ ደግሞ በ85 ሚሊዮን ዶላር የገዛ ሲሆን፣ ከጠቅላላ ክፍያው 30 በመቶውን ከ40 ቀናት በፊት የተቀረውን 70 በመቶ ከሁለት ሳምንት በፊት ከፍሎ አጠናቋል፡፡

ሄኒከን ምርቶቹን ወደ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ1900 መላክ መጀመሩ ሲታወስ፣ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ፋብሪካ እ.ኤ.አ. በ1923 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ ገንብቷል፡፡ ሄኒከን አፍሪካ ውስጥ 30 የቢራና ሁለት የብቅል ፋብሪካዎች ሲኖሩት፣ በ20 አገሮች ውስጥም እንደሚንቀሳቀስ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሄኒከን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት የጀመሩት አቶ ሰለሞን ግዛው (ሶል ሄኒከን) የተባሉ አስመጪ ነበሩ፡፡ ሥራውን እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም. እንደጀመሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሄኒከንን ያስለመድኩት ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ በመሸጥ ነው፡፡ በአንድ ኮንቴይነር ጀምሬ ቀስ በቀስ ወደ ስድስት ኮንቴይነር በዓመት ማስመጣት ደርሼ ነበር፤›› ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ሥራውን እ.ኤ.አ በ2010 ለካንጋሮ ግሩፕ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡

ሐረርና በደሌ ፋብሪካዎች የተዋቀሩት በአክሲዮን ማኅበር ሲሆን፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ሄኒከን ፋብሪካዎቹን በአክሲዮን ማኅበር ደረጃ ይዞ እንዲቀጥል አስገድዶታል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ ሄኒከን የቤተሰብ የንግድ ተቋም በመሆኑ ፋብሪካዎቹን ከአክሲዮን ማኅበር ወደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ መቀየር ፈልጎ ነበር፡፡ ይሁንና ሕጉ አልፈቀደለትም፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ለሚስተር ዲማን ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ሕጎችን እናከብራለን፡፡ በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ጋር መምከር ይኖርብናል፡፡ ይህ መፍትሔ ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ በየነ በበኩላቸው ፋብሪካዎቹ በአክሲዮን ማኅበርነት ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

የባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ በያዝነው ዓመት 18 የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሸጦ 1.8 ቢሊዮን ብር ገቢ አድርጓል፡፡ ሄኒከን በተጨማሪ የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ለመግዛት በመጫረት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቃለየሱስ በቀለ

ምንጭ ሪፖርተር

Advertisements

What do you say about this? እርስዎ ምን ይላሉ?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s