Uncategorized

“ድንግል ማርያም ” ነኝ ባይዋ ሴት ክስ ሊመሰረትባት ነው

“ የሥላሴ መንፈስ በእኔ ላይ አድሯል፣ ከእግዚአብሔር የተላክሁ ማርያም ነኝ” በሚል ድንኳን በመኖሪያ ቤቷ አካባቢ ተክላ ተከታዮች ስታፈራና እምነቷን ስታስፋፋ የነበረችው ሴት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተካሄደባት ነው፡፡

በአምቦ ከተማ ገላን በተባለ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ተወልዳ በ1994 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ትዕግስት ብርሃኑ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ “ማርያም ነኝ” በሚል ማሳሳቻ ተከታዮችን አፍርታ እንደነበር ከፖሊስ የተገኘ ማስረጃ ይጠቁማል፡፡

በዚሁ አመት የፋሲካ በዓል ሰሞን “እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቼ በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ” በማለት ዝግጅት የጀመረችው ትዕግስት፣ የስቅለት ዕለት የሾህ አክሊልና የምትሰቀልበትን መስቀል አዘጋጅታ ጀርባዋን እንደ ተገረፈች ታውቋል፡፡

በመስቀሉ ላይ መሰቀሏን ያየ ግን አልተገኘም፡፡ በሦስተኛው ቀን ትዕግስት ከሞት ተነሳች ተብሎ ለአካባቢው ህዝብ እንደታየች ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የት ደርሳ እንደመጣች የጠየቃት ስለመኖሩ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡ አብረዋት ይኖሩ የነበሩት አባቷ አቶ ብርሃኑ ድርጊቷን አጥብቀው ይቃወሙ እንደነበር የሚናገሩ ምንጮች ጠጥተው ቤት ሲገቡ በጉዳዩ ይነታረኩ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ አባቷ ግን የልጃቸውን መለኮታዊ ነኝ ባይነት ማስቆም አልቻሉም፡፡ ትዕግስት ይባሱኑ “የሥላሴ መልዕክተኛ ድንግል ማርያም ነኝ” ማለት ጀመረች ይላሉ- ምንጮች፡፡

በዚህ አድሯጎቷ የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ ተቃውሞውን በማሰማት ከአካባቢው አባረራት፡፡ ትዕግስት በዚህ ጊዜ ወንጪ ገዳም እንደገባች የገለፀው ፖሊስ፣ ሀይለገብርዔል ከተባለው ተከታይዋ ሦስተኛ ልጇን እንደወለደች ይናገራል፡፡ ከወንድ ጋር ተገናኝታ እንደማታውቅ የምትናገረው ትዕግስት፣ ሦስቱንም ልጆቼን በመንፈስ ቅዱስ ነው የወለድኳቸው ባይ ናት፡፡ የመጀመሪያ ባለቤቷም ይሄንኑ ይመሰክራል- ከእሷ ጋር ስጋዊ ግንኙነት ፈፅሞ እንደማያውቅና ሁለት ልጆቿን በመንፈስ ቅዱስ እንደወለደቻቸው በመናገር፡፡

ትዕግስት በወንጭ ገዳም ሳለች የሥላሴ መልዕክተኛ ነኝ ማለቷን- ገፍታ ቀጠለችበት፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላ ጉድ መከሰቱን የሚናገሩ ምንጮች፣ እናቷ ወይዘሮ ባይሴ ኡዊሳ (በክርስትና ስማቸው ወለተ ሥላሴ) ነሐሴ 25/2000 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ሞተው እንደተገነዙ፣ ከዚያም የዚያኑ ዕለት ከምሽቱ 4 ሰዓት ከሞት ተነሱ ተብሎ እንደተዋራ ይናገራሉ፡፡ እናት ከሞት የተነሱት ከሰማይ የተላኩትን መልዕክት ለማድረስ እንደሆነ ገልፀው “ወ/ሮ ትዕግስት ወይም በክርስትና ስሟ ምስለ ፍቅር ኢየሱስን ስሟት ተብላችኋል” ካሉ በኋላ በነጋታው ተመልሰው እንደሞቱና ነሐሴ 27/2000 የቀብራቸው ሥነስርዓት እንደተፈፀመ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ግን መቃብራቸው ተከፍቶ እንዳረጉ ነው ልጃቸው ትዕግስት የተናገረችው፡፡

ነሐሴ 29/2000 ዓ.ም ሌሊት ላይ ነጎድጓድ መብረቅ ሰምቶ ከጥበቃ ክፍሉ እንደወጣ የሚናገረው የገዳሙ የጥበቃ ሰራተኛ፣ የትዕግስት እናት መቃብር ላይ መላዕክት እንዳየ ለፖሊስ ገልጿል፡፡ በእጁ አብርቶ ይዞት የነበረው ባትሪ መጥፋቱንና መብረቁ ገፍትሮ እንደጣለው ለፖሊስ የገለፀው የጥበቃ ሠራተኛ በድንጋጤ ወደክፍሉ ተመልሶ እንደገባ ተናግሯል፡፡ ሲነጋጋ ሁኔታውን ለማጣራት ወደ መቃብሩ ሲሄድ የወለተ ሥላሴ መቃብር ለሁለት ተከፍሎና መሃሉ ተሰንጥቆ፣ የአስከሬን ሳጥኑ ባዶ ሆኖ ማየቱን በሰጠው ቃል ገልጿል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ትዕግስት “የዓለም ፍፃሜ ደርሷል፣ ንስሃ ግቡ” እያለች መስበክ መጀመሯን ምንጮች ይናገራሉ፡፡

ሴትየዋ የተቀበሩበት ስፍራ ታጥሮ በሰዎች እየተጎበኘ እንደሆነ የጠቆመው ፖሊስ፣ ሁኔታው የማጣራት ስራ እንደሚፈልግም ይናገራል፡፡

በረቡዕ ቀን በሬና በግ አርዳ ነዋሪዎች በፆም ቀን ሥጋ እንዲበሉ ማስገደዷ ከነዋሪው ጋር ለተፈጠረው ግጭት መንስኤ ሲሆን፣ የፆም ቀን ቢሆንም አብርሃም ቤትም በሬ ተጥሎ ለሰዎች የመገበው ሐምሌ ሰባት እንደሆነ በመፅሃፍ ቅዱስ ተፅፏል በማለት ሐምሌ 7/2002 ዓ.ም ነዋሪው ሥጋ እንዲበላ፣ ካልበሉ ግን ምድር ተከፍታ እንደምትውጣቸው ታስፈራራ ነበር ተብሏል፡፡

ሥጋውን የበላ ይማራል በማለቷ ግማሹ ነዋሪ ቢበላም ግማሹ አልበላም እንዳለ የጠቆሙ ምንጮች፣ በዚህም ምክንያት ትግስት ከአካባቢው ለቅቃ አዲስ አበባ እንደገባች ይናገራሉ፡፡

አዲስ አበባ ከተከታዮቿ አንዷ በሆነችው ሃና ብሩክ በተባለች ግለሰብ መኖሪያ ቤት (ሳር ቤት አካባቢ) ያረፈችው ትዕግስት፣ ከየት እንደመጡ ያልታወቁ 16 ህፃናትና ጎልማሶች አብረዋት ይኖሩ እንደነበር ታውቋል፡፡ ህፃናቱን ለልመና ተግባር ትጠቀምባቸው እንደነበር የጠቆመው ፖሊስ ፣ እሷን ተከታይ እንደሆኑና ደረታቸውን በድንጋይ እንዲደለቁ ታደርጋቸው እነደነበር እንዳረጋገጠ አመልክቷል፡፡

አብዛኞቹ ተከታዮቿ ራሳቸውን የማያውቁና ከትክክለኛ አእምሯቸው እንደተለዩ የሚናገረው ፖሊስ፣ የሴትየዋ ድርጊት የተጋለጠው ህፃናቱ ለጎረቤት “እመብርሃን ናት፣ ደሟን እየቀዳች የክርስቶስ ደም ነው እያለች ታጠጣናለች” ብለው ከተናገሩ በኋላ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በመጠቆም ወ/ሮ ትዕግስት ብርሃኑ በቁጥጥር ስር እንደዋለች ገልጿል፡፡

በወቅቱ ፍተሻ አለመካሄዱን የጠቆመው ፖሊስ፣ ህፃናቱ የት እንዳሉ እንደማያውቅና ምርመራ ላይ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ከሦስት ዓመት በፊት ከተከታዮቿ አንዷ የነበረችው የ19 አመቷ ትዕግስት ያለው ለስምንት ቀን ያለምግብ በመቆየቷ፣ ደረቷን በድንጋይ እንድትደልቅና የተበጠበጠ ምንነቱ ያልታወቀ ቅጠል እንድትጠጣ በመደረጉ ህይወቷ እንዳለፈ ገልጿል፡፡ የወጣቷን አስከሬን በማውጣት የአማሟቷን ሁኔታ ለማጣራት ከህክምና ባለሙያዎች ጋር አየተመካከረ እንደሆነም ፖሊስ አክሎ ገልጿል፡፡

ከወ/ሮ ትዕግስት ብርሃኑ ጋር በተያያዘ ትዳራቸው የፈረሰ፣ ንብረታቸውን ያጡ ግለሰቦች እንዳሉም የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል፡፡

አዲስ አበባ ቤቴል የተባለው ሰፈር ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ አለሚቱ በትዕግስት በደል እንደደረሰባት ቃሏን ለፖሊስ ሰጥታለች፡፡ ቤተሰቦቿ ወደ አምቦ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጉደር ከተማ የወሰዷት፣ ወ/ሮ ትዕግስት በፀበል ከህመምሽ ትፈውስሻለች በሚል እንደሆነ የተናገረችው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ከተጠመቀች በኋላ ከቲቢ ካንሰር ተፈውሰሻል ብለው ህዝብ ተሰብስቦ በቪዲዮ እንደተቀረፀች ለፖሊስ ገልፃለች፡፡

ከዚህም በኋላ ደግሞ ልጆቼንና ወርቄን ነጥቃኛለች የምትለው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ልጆችሽ የእኔ እንጂ የአንቺ አይደሉም መቧሏን ትናገራለች፡፡ “ አንድ ቀን የትንሿን ልጄን ፀጉር ሳበጥር ለምን ነካሻት ተብዬ እስከምዝለፈለፍ ድረስ ተደብድቤያለውሁ” ትላለች፡፡

ከእኔ የትም አታመልጡም ስለምትል ሁሉም ይፈራታል የምትለው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ተከታዮቿ “ እመቤታችን ናት አምልኳት” እንደሚሉ ትናገራለች፡፡ “በምስል ታመልካላችሁ፤ ይሄው በአካል መጥታለች አምልኳት” ይሉናል ብላለች፡፡ በየቀኑ ፆም አለ፣ በቀን አንዴ ንፍሮ እንበላለን ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ፆሙ የአዋቂ ብቻ ሳይሆን ከስድስት ወር ጀምሮ ያለ ህፃንም እንዲፆም ይደረጋል- ለሦስት ቀን ጡት አይሰጠውም ብላለች፡፡

ወ/ሮ ትዕግስት ትምህርት ሃጢያት ነው በሚል አቋም ልጆች እንዳይማሩ እንደምታደርግም ተበዳይዋ ለፖሊስ ተናግራለች፡፡ የ12 ዓመት ልጄን ከዚህ እንግልት ለማዳን እንጥፋ ብዬው ነበር ፣ እሱ ግን ፈርቶ እምቢ አለኝ የምትለው- አለሚቱ፣ የባሰው መከራ የመጣው ግን የ3 አመት ልጄ ለ3 ቀን ያለ እህል ውሃ ፆም ፀሎት መያዝ አለበት ስትላት እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ትልቁ ልጄ አሻፈረኝ ስላለ ሌላ ሙከራ ባደርግ ይገሉኛል ብዬ ትንሿን ልጄን ይዤ ጠፋሁ ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ የወንድ ልጇ ነገር ስላላስቻላት ተመልሳ ወደ አምቦ መሄዷን ትናገራለች፡፡

ሆኖም ሰው ሁሉ ስለጠላቸው ወደ አዲስ አበባ ሄደዋል ተብላ መመለሷንና ልጇን ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማግኘቷን ገልፃ ለሳምንት ያህል አብሯት ከቆየ በኋላ እንደጠፋ ገልጻለች፡፡ ፖሊስ ልጇን ለሁለተኛ ጊዜ አግኝቶ የሰጣት ቢሆንም ተስማምተው ሊኖሩ እንዳልቻሉ እናት ትናገራለች፡፡ እኔን እንደ እናቱ ሳይሆን እንደ ጠላት ነው የሚያየኝ ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ “ ማርያምን ከሰሻት እኔ ካንቺ ጋር አልኖርም” ይላት እንደነበር ገልፃለች፡፡ ልጄ “ እኛ ምድራዊ አይደለንም፣ ሰማያዊ ነን” እያለ እሷ የምትናገረውን ሲደግም ነገሩ ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ስለገባኝ ወደ እነሱ እንዳይመለስ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተደርጓል የምትለው እናቱ አሁን ትንሽ ቢሻሻልም፣ እሷን ግን እንደጠላት እንደሚመለከታት ትናገራለች፡፡ ልጄ ጤነኛ አይደለም ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ንብረቴን በሙሉ አጥቼአለሁ ከምንም በላይ የሚፀፅተኝ ግን ልጄን ማጣቴ ነው ብላለች- እንባዋን እያፈሰሰች፡፡

ወ/ሮ ትዕግስት አበራ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ ስትሆን ጉዳይዋ ወደ ፍርድ ቤት ተልኮ በጊዜ ቀጠሮ ላይ ነው፡፡  ወ/ሮ ትዕግስት ለፖሊስ በሰጠችው ቃል “ የሥላሴ መልዕክተኛ ነኝ፡፡ እኔ ከወንድ ጋር አልተኛሁም፤ ተርፌሳም፣ ማርያምን ዮሴፍ ይጠብቃት እንደነበር ጠባቂዬ ነው፡፡ ሦስት ልጆች ቢኖሩኝም በመንፈስ ቅዱስ ነው የወለድኳቸው፣ ይህንን ሁሉ ያደረኩት ሥላሴዎች አዘውኝ ነው፣ አላጠፋሁም” ብላለች፡፡

ምንጭ (ሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ -ሰላም ገረመው)

More Articles From Ethiopian observer’

እኔ እምለው ኢትዮጵያውያን አንድ እንዳይሆኑ ተረግመዋል እንዴ? Are Ethiopians cursed not to be one

የኦጋዴን የነዳጅ ይዞታዎች ለቻይና ኩባንያ ተሰጡ

Advertisements

One thought on ““ድንግል ማርያም ” ነኝ ባይዋ ሴት ክስ ሊመሰረትባት ነው

 1. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
  ‹‹እስከ መጨረሻ የሚፀና ግን እርሱ ይድናል፡፡›› ማቴ 24-13
  ሰሞኑን አንድ ነገር በ ፌስ ቡክ የመረጃ መረብ ላይ ሳነብ በመጀመሬያ ˝ ወቼ ጉድ ˝ ከማለት የዘለለ ምንም አላልኩም ነበር፡፡ በኃላ ላይ ግን ብዙ ሰዎች አስተያየት ሲሰጡ ሣይ ግን ˝ምን ይሆን ይሔ ነገር˝ በማለት ሥሜት ተከታተልኩት፡፡ በሕይወት ዘመኔ እንደዚህች ቀን ደንግጬ እና አዝኜ የማውቅ አይመስለኝም፡፡
  ወገኞቼ እውነት በእኛው ሀገር በኢትዮጵያ ነው ይሕ ጉድ የተፈፀመው? በእኛዋ ቤተ ቅድስት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ? አረ ውሸት ነው በሉኝ ወገኖቼ፡፡ እያወራሁ ያለሁት ሎቱ ስብሐት እና ˝ ማርያም ነኝ ˝ ብላ ስለተነሳችው ጉድ ነው፡፡
  አመቱን ሙሉ ስብሐተ እግዚአብሔር በሚደርስባት ሀገር፤ የእመቤታችን እስራት ርስት በሆነች ሀገር፤ የታላቁ አባት የቅድስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሀገር፤ የቅዱሳን ዋሻ በሆነች ሀገር፤ ሰማያዊ የሆነውን የቅዱስ ያሬድን ዝማሬ ዘወትር በምታቀርብ ሀገር….በኢትዮጵያ ውስጥ ነው ይህ ጉድ የተወራው?
  እሺ አሁን ምን እናድርግ?
  እንደ ባለፉት አመታት ሎቱ ስብሐት እና ˝ አምላክ ነኝ˝ ብሎ ብዙዋችን ሲያሰግድ እና ሲያሳስት እንደነበረው ታምራት ዝምብለን ስቀን ቀልደን እንለፍ? ወይስ ‹‹ የዓለም ›› መጨረሻ ስለደረሰ ምንም ማድረግ አይቻልም ብለን ዝም ብለን እንቀጥል? ወይስ ሴትየዋ ርኩስ መንፈስ ያደረባት ስሆነች ይህ ማለት ምንም አይደል ብለን እንቀጥል?
  ወይስ
  ማቅ ለብሰን፡ ትቢያ ነስንሰን ‹‹ አቤቱ ማረን ›› እንበል? የመንግስት ያለህ ፡የሕግ ያለሕ እንበል? በእውነት የዘመኑ ፍፃሜ መድረሱን አውቀን ራሳችንን በንስሃ ስሙና አጥበን፡ ክቡር ስጋውን በልተን፡ ቅዱስ ደሙን ጠጥተን ለመንግስቱ ለመዘጋጀት ቆረጥን?
  ያም ሆነ ይሕ ፡ በቀልድ አለፍነውም ሆነ አስተዋልነው፡ በእውነት የሕ ነገር ተፈፅሞዋል፡፡ እንዲሁም ሌሎች በማቴ 24፤ 3-8 ያሉት ትንቢቶች በሙሉ ተፈፅመዋል፡፡እየተፋፀመም ነው፡፡ ታድያ ምን ይሆን የሚቀረው?
  እባካችሁ በአንድነት ሆነን ከልብ እንጩህ፡ የትንቢትህ መፈፀሚያ አንሁን፡ ስለ ቅድስ ድንግል ማርያም፡ ስለ መጥምቀ መለኮት ቕዱስ ዮሐንስ ፡ ስለ ቅዱሳኖች ብለህ ማረን እንበል፡፡ እባካችህሁ እንመለስ፡፡ ልቦናችንን አናስጨክነው፡ የጭንቅ አማላጅዋን ‹‹ እባክሽን አስራት ሀገርሽን ኢትዮጵያን እንዲሁም ቅድስ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ከርስቲያናችንን ጠብቂልን ›› እንበላት፡፡
  ምን ትላላችሁ ወገኖቼ?
  ‹‹እንግዲህ በነብዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት ፡በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ ÷ አንባቢው ያስተውል›› ማቴ 24-15
  አቤቱ የቅዱሳን አምላካቸው እግዚአብሔር ሆይ በቸርነትህ ገፀ ምሕረትሕን መልስልን፡፡ አሜን!!!

  ወስብሃት ለእግዚአብሔር

What do you say about this? እርስዎ ምን ይላሉ?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s