Uncategorized

ለመጨረሻ ጊዜ ታክሲ ውስጥ ቁጭ ብሎ ፎቶ መነሳት አዋጭ ሊሆን ነው እንዴ???

እናንተዬ በጣም እኮ የሚገርም ነው! ኑሮ እየወፈፈ ነው ወይስ እየከነፈ? ባለፈው ለእንቁጣጣሽ በ500 ብር የገዛሁት በግ አንድ ሸክላ ድስት እንኳን አይሞላም፡፡ በእኔ ቤት ብዙ ብር ስላወጣሁ ትልቅ በግ የምገዛ ነበር የመሰለኝ፡፡ በአመት ባዕላዊው የስጋ ገበያ ግን አሁን የእኔ 500 ብር ምንም ነው፡፡ ይህን ለማስረገጥ ደግሞ ከጥቂት አመታት በፊት አባቴ በገዛው የ20 ብር ዶሮ የሚጨናነቀው የእናቴ ሸክላ ድስት እኔ ለገዛሁት በግ መስፋቱን ከበቂ በላይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የምሬን እኮ ነው፡፡ በጉ ባይታረድ ኖሮ ከነ ነፍሱም ቢገባ ተደላድሎ ሸክላ ድስቱ ውስጥ ለመተኛት ምንም ያህል አይጨናነቅም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ከአሁን በኋላ በግ የሚባል ነገር ላልገዛ ወስኛለሁ፡፡ ግልግል ነው፡፡

እናላችሁ ከገንዘቤም ሳልሆን ከስጋውም ሳልሆን ያሳለፍኩት እንቁጣጣሽ በኪሴ ውስጥ ከፈጠረው ጣጣ ፈንጣጣ ሳልገላገል ያ መከረኛ  የታክሲ ዋጋ  በሆነ  ምክንያት  አገርሽቶ በየእርቀቱ  15 ሣንቲምና  ከዛ  በላይ  ጨመረ፡፡ ጭማሪው ተደማምሮ ተደማምሮ ወርሃዊ የታክሲ በጀቴን ወደ 412 ብር ከፍ እንዳደርግ ያስገድደኛል፡፡ ይህም  “ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት የታክሲ በጀት ጋር ሲነፃፀር” የ10.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የአሁኑን የታክሲ ዋጋ ጭማሪ ከበፊቶቹ ለየት ያለ ነው፡፡ የበፊቶቹ ከነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ጭማሪዎች ሲሆን የአሁኑ ግን ከነዳጅ ጭማሪ ጋር በቀጥታ የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡

ያም ሆነ ይህ ከዘርፈ ብዙ ዋና ዋና የኑሮ ቀዳዳዎቼ አንዱ በሆነው የትራንስፖርት ወጪዬ ላይ 10.5 በመቶ ጭማሪ፡፡

በዚህ ጉዳይ እየተወዛገብኩ ዛሬ ጠዋት ከቤቴ ስወጣ የአንድ ተሳፋሪና የታክሲ ረዳት ውዝግብ ሳልወድ በግዴ አሳቀኝ፡፡ ሰውየው ታክሲ መጨመሩን አልሰማም መሰለኝ፡፡ ከአየር ጤና ሜክሲኮ ለመጓዝ ከኪሱ 4 ብር አውጥቶ ይሰጥና መልስ ቢጠብቅ ዝም፤ ቢጠብቅ . . . ቢጠብቅ . . .ረዳቱ ጭራሽ እረስቶታል፡፡ ከዛ ሰውየው “መልሴን ስጠኝ እንጂ” ሲለው ረዳቱ 10 ሳንቲም ይመልስለታል፡፡ ተሳፋሪው በግራ መጋባትና በንዴት  “ስማ ታክሲውን ኮንትራት አይደለም እኮ የያዝኩት ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ ሜክሲኮ 3.90 የገባው ” ይለዋል፡፡ የረዳቱ መልስ ግን አጭር ነበር “መክፈል ካልቻልክ ወርደህ እቤትህ ቁጭ በል፡፡ ታክሲ ጨምሯል”፡፡ በሳቅ ፍርስ ነው  ያልኩት፡፡ ማሽላ እያረረ ይስቃል . . . ደሞስ እስከመቼ እቤት ቁጭ ብሎ ይገፋል፡፡ ከቤት መውጣት እኮ የግድ ነው፡፡

ወይ ጣጣ . . . ሰሞኑን ደግሞ የአከራዬ አስተያየት አላማረኝም፡፡ ስገባ ስወጣ እጅ እጄን፤ ኪስ ኪሴን ማየት ጀምረዋል፡፡ የሆነ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ የቤት ኪራይ ወጪዬ ደግሞ በስንት በመቶ ሊያድግ ይሆን?

አንድ ተጫዋች ቢጤ የፌስቡክ ጓደኛ አለኝ፡፡ ማህበራዊ ድረ ገፁ ላይ ስንገናኝ “How is Life?” ስለው “Life is getting knife?” ይለኛል፡፡ ኑሮ እንደቢላዋ አየሆነብኝ ነው ማለቱ ነው፡፡ ለነገሩ ልክ ነው በስንት መከራ የምትገኝ ወርሃዊ ገቢውን እነ አስቤዛ፣ ታክሲ፣ የቤት ኪራይ ወዘተ ሙዳ ሙዳዋን እየጎመዱላት አልበቃ ብትለው ነው፡፡

ለማንኛውም ከአሁን በኋላ ባለ ሰማያዊ ቀለም ታክሲ ውስጥ ተሳፍረው ሲሄዱ ፎቶ መነሳት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ለትውስታ! ማን ያውቃል ታክሲ ውስጥ ቁጭ ብሎ የተነሱት ምስል የፎቶ አልበም ማድመቂያ የሚሆንበት ጊዜ እየቀረበ ስለመሆኑ፡፡እኔ በበኩሌ ከትንሽ ጊዜ በኋላ በታክሲ መሄድ ሳይናፍቀኝ የሚቀር አይመስለኝም፡፡

እዚህ ጋር የሆነ ጋዜጣ ሳነብ ያገኘሁትን የኔን መሰሉ ሰውዬ ታሪክ ልንገራችሁማ…. ሰውየው ህይወት በየቀኑ የምትጭንበት ሸክም ከመክበድ አልፎ እያጎበጠው ያለ አይነት ሰው ነው፡፡ እና በየጊዜው መቀነስ ይቅርና ባለበት መርጋት እንኳን ላቃታቸው ሸቀጦች መወደድ ፈጠራ የታከለበት ምላሽ ነበር የሚሰጠው፡፡ ለዓለም አቀፍም በሉት ሀገር በቀል ችግር ሀገር በቀል መፍትሄ መሆኑ ነው፡፡

“የቅንጦት ሸቀጦች” ይላቸዋል ግለሰቡ እነዚህን ዋጋቸው አልቀመስ ያለውን ነገሮች ሁሉ፡፡ እናላችሁማ ሰውየው የስኳር ዋጋ ሲጨምር ስኳር የቅንጦት ነው ብሎ እጅግ የሚጎመዝዝ ቢሆንም ሻይን ያለስኳር ይጋተረው ገባ፡፡ ዘይትም ሲወደድ ዘይት የቅንጦት ነው ብሎ ዘይት አልባ ሹሮ መብላት ቀጠለ፡፡ እንዲያ እንዲያ እያለ ዋጋቸው አልቀመስ ያለውን ነገሮች ሁሉ እየተወ ከእነሱም እየሸሸና እራሱን እያገለለ ለመኖር ቢሞክርም ኑሮ በጠቅላላው ሲወደድበት ምን ቢያረግ ጥሩ ነው? በቃ መኖር የቅንጦት ነው ብሎ . . . ( ህይወት የሌለው ኑሮ መኖር ጀመረ)

እኔ ግን ይሄንን በፍፁም አልሞክረውም፡፡ “ ከመሞት መሰንበት” ትላልች አያቴ፡፡ መኖር ብዙ ያሳያል . . .

https://ethiopianobserver.wordpress.com

More Posts from Ethiopian Observer

Advertisements

3 thoughts on “ለመጨረሻ ጊዜ ታክሲ ውስጥ ቁጭ ብሎ ፎቶ መነሳት አዋጭ ሊሆን ነው እንዴ???

  1. አይዞን ወንድሜ ኪስ ከሚያይ አከራይ
    ኪስ ከሚያራቁት ታክሲ
    የሚጠብቅ…(እንትን…ምን ነበር እሱ….ማን ነበር ይህን ማድረግ የሚችለው)……ይስጠን
    ሌላ ምን ይባላል?

  2. Pingback: ስንት ሰው ባዶ እግሩን በሚዳክርባት ሀገር ስለ ሩኒ ጫማ አውልቆ በካልሲ መሄድ ማውራት ስድብ አይደለምን | Ethiopianobserver

What do you say about this? እርስዎ ምን ይላሉ?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s