Uncategorized

የሆስተሷን ዓይን ያጠፋው ተጠርጣሪ ተከሰሰ

‹‹ድርጊቱን ፈድሜያለሁ ጥፋተኛ አይደለሁም››  ተጠርጣሪ ተከሳሽ የቀድሞ ባለቤቷ 

የተጠየቀበት አንቀጽ ዋስትና ስለማይከለክል መብቱ ይጠበቅለት”  የተጠርጣሪ ተከሳሽ ጠበቆች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ዋና አስተጋጅ ሆስተስ አበራሽ ኃይላይን መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ሁለት ዓይኖቿን ባልታወቀ ስለት አጥፍቷል በሚል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር በዋለው የቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍስሐ ታደሰ ላይ ጥቅምት 7/2004 ዓ.ም ክስ ተመሠረተ፡፡

ዓቃቤ ሕግ ሁለት ክሶችን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበ ሲሆን፣ በመሠረተው በመጀመርያው ክሱ ላይ እንደገለጸው፣ ተከሳሹ ሰው ለመግደል በማሰብ መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ወደ ተጐጂ፣ ቤት ስልክ ደውሎ ሊያገኛት እንደሚፈልግ ይገልጽላታል፡፡ ወደ ቤቷም ሄዶ አብረው ቆይተዋል፡፡ ተከሳሽ MP09472 እስታርተር ሽጉጥ በማውጣት በተጐጂዋ ላይ ይደቅናል፡፡ በማስፈራራት እንድትቀመጥ ያደርጋል፡፡ ጉሮሮዋን አንቆ በያዘው ሽጉጥ ደጋግሞ ጭንቅላቷን በመደብደቡ ትወድቃለች፡፡ እንደወደቀች ምንነቱ ያልታወቀ ስለት ነገር ከኪሱ በማውጣት ዓይኗን ጐልጉሎ በማውጣት ተዝለፍልፋ ስትወድቅ የሞተች መስሎት ራሱን ለፖሊስ አሳልፎ በመስጠቱ፣ በፈጸመው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ተከሷል፡፡ 

ሌላው ተጠርጣሪው የተከሰሰበት ወንጀል በአንደኛ ክሱ ላይ የተጠቀሰውን ሽጉጥ ከአምስት ጥይቶች ጋር ይዞ በመገኘቱ፤ የተከለከለ ጦር መሣርያን በመያዝ በወንጀል መከሰሱን የዓቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር ያስረዳል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪ ተከሳሹ ላይ አምስት የሰው፣ ስድስት የጽሑፍና አንድ ኤግዚቢት ከክሱ ጋር አያይዞ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዕለቱን ችሎት ከመጀመሩ በፊት፣ ችሎቱን ለመከታተል በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ የሞሉት በርካታ ሰዎች፣ ኡኡታና ጩኸት በመስማታቸው ሁሉም ወደ ችሎቱ እንዲገቡ አዘዘ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ጠባብ በመሆኑ ችሎቱ የተሰየመው ወደ አንደኛ ወንጀል ችሎት በመቀየር ስለነበር፣ ከመቶ የሚበልጡ ታዳሚዎች ተቀምጠው ችሎቱን ሊከታተሉ የሚችሉ ቢሆንም፣ ዳኛ ሸምሱ ሲርጋ ‹‹ሁሉም ይግቡ›› በማለታቸው፣ ሁሉም ታዳሚ ችሎቱን ቆሞ ለመከታተል ተገዷል፡፡

“ማንም ምንም ቢል ከሕግ በላይ መሆን አይቻልም፡፡ የምንሠራው ሕጉን ብቻ ተከትለን ነው፡፡ መጮህ የሚጨምረውም የሚቀነሰውም ነገር የለም፡፡ ችሎት ከመረበሽ ያለፈ ፋይዳ ስለሌለው በፀጥታ ተከታተሉ፡፡ ጩኸት ሌላ ችግር ሊያስከትል ይችላል፤” በማለት ፍርድ ቤቱ ለታዳሚው ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ሥራውን ጀመረ፡፡ ፍርድ ቤቱ በዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን ክስ ካነበበ በኋላ የተከሳሽ ጠበቆች በክሱ ላይ ተቃውሞ ወይም የሚናገሩት ካለ እንዲናገሩ ዕድል ሰጠ፡፡

የደረሳቸው ክስ ያልተፈረመበት መሆኑን ጠቁመው ደንበኛቸው የተከሰሰበት አንቀጽ በሞት የሚያስቀጣ መሆኑን በመግለጽ፣ መቃወሚያ ማቅረብ የሚችሉት አስበውበትና ደንበኛቸውም የእምነት ክህደት ቃሉን እንዴት መስጠት እንዳለበት ለማማከር አጭር ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠበቆቹ ጠየቁ፡፡

የጠበቆቹን ጥያቄ በመቃወም ምላሽ የሰጠው ዓቃቤ ሕግ፣ ጠበቆቹ ያቀረቡት ሐሳብ በወንጀል ሕጉ ያልተቀመጠ በመሆኑና እነሱም በግልጽ እየታየ በፍርድ ቤት ሲካሄድ የነበረን ሒደት ምክክር ያሻዋል ማለታቸው አግባብ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረዳ፡፡

ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን መቃወሚያ ወድቅ በማድረግ ለጠበቆቹ የተወሰነ ደቂቃ በመስጠት ከተከሳሹ ጋራ ተመካክረው እንዲመለሱ በዳኞች ጽሕፈት ቤት በኩል ወደ ውጭ እንዲወጡ ፈቀደ፡፡

ጠበቆች ከደንበኛቸው ጋር ከተመካከሩ በኋላ ተመልሰው ባቀረቡት መቃወሚያ፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የጠቀሰው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥር ከክሱ ዝርዝር ጋራ አብሮ እንደማይሄድ፣ በክሱ ላይ “በቤት ውስጥ ከቆዩ በኋላ ድብደባ ተነሳ” ቢልም ምክንያቱን አለማስቀመጡን፣ እንዲሁም “የሞተች መስሎት ራሱ እጁን ለፖሊስ ሰጠ” የሚለው ዓቃቤ ሕግ ቀድሞ ክሱን ከወዲሁ ደምድሞ ማቅረቡን ስለሚያሳይ፣ ክሱ በአንቀጹ መሠረት እንዲስተካከልለት ፍርድ ቤቱን ጠየቁ፡፡

ተከሳሹ ሽጉጥ ይዞ ከመገኘቱ ውጭ የት ይዞ እንደተገኘ የዓቃቤ ሕግ ክስ ስለማያመለክት የጠቀሰው አንቀጽና ያቀረበው የክስ ዝርዝር ስለማይጣጣም ክሱ እንዲሻሻልላቸው ጠበቆቹ በድጋሜ ፍርድ ቤቱን ጠየቁ፡፡

ጠበቆቹ ያቀረቡት መቃወሚያን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ እንደገለጸው፣ ጠበቆቹ ያቀረቡት መቃወሚያ በወንጀል ሕጉ 130 መሠረት ነው፡፡ ግን የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ የሚያመለክተው በወንጀል ሕጉ 132 ሀ እስከ ሰ ድረስ ያለውን ብቻ ነው ማቅረብ ያለበት፡፡ በዚህ መሠረት ተቀባይነት የለውም፡፡ ይኼ ከታለፈ ሁሉም ነገር በማስረጃ የሚረጋገጥ በመሆኑ ማስረጃ ከመሰማቱ በፊት ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ይደረግ፡፡ ሽጉጡን በሚመለከት በማስረጃ የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡ የወንጀል ሕግ 539 በዝርዝር እንደሚገልጸው አስቀድሞ ማሰብና ግድያ ሙከራ ማድረግ ይገናኛሉ፡፡

ፍርድ ቤቱ የጠበቆቹን የመቃወሚያ ቃል ውድቅ በማድረግ ተከሳሹ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጡ አዘዘ፡፡ ተጠርጣሪ ተከሳሽ ፍስሐ በሰጠው የእምነት ክሕደት ቃል፤ “ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ ወንጀለኛ ግን አይደለሁም፤” አለ፡፡ ፍርድ ቤቱ በመካከል ገብቶ “ለምን ጥፋተኛ አይደለሁም አልክ?” ሲለው፣ “በወቅቱ የሆነውን ነገር አላስታውስም፤ አብረን ጠጥተናል፤ አብረንም ወድቀን ነበር፤ ከዚያ በኋላ ሄጄ ፖሊስ ስጠራም እንደምታሰር አላውቅም ነበር፤›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ጠበቆቹም የተጠቀሰበት የሕግ አንቀጽ ዋስትና ስለማይከለክል የዋስ መብቱ እንዲከበርለት ጠየቁ፡፡

የተከሰሰበት አንቀጽ ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ መሆኑን በመጥቀስ፣ በወንጀል ሕጉ 63 መሠረት የዋስ መብቱን እንደሚቃወም ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ አመለከተ፡፡ ግለሰቡ በዋስ ቢወጣ አቅም ስላለው በተለያየ መንገድ ከአገር እንደሚወጣና በወንጀል ሕጉ 67 መሠረትም ማስረጃ ሊያጠፋበት እንደሚችል ገልጾ በድጋሚ የጠበቶቹን ጥያቄ ተቃወመ፡፡

የወንጀል ሕጉ 63 ከ15 ዓመት በላይ የሚታሰርን የዋስ መብት እንደማይከለክል፣ የሚከለክል ቢሆን ኖሮ 15 በመቶ የሚሆነው የሕግ ተጠያቂና ከ15 ዓመት በላይ ይታሰር እንደነበር፣ ነገር ግን ዋስትና የሚከለክለው በጠባቡ ከ15 ዓመት በላይ በሚያሳስር የሕግ አንቀጽ የተከሰሰ የሚያሳስርና ተጐጂው ከሞተ ሊከለከል እንደሚችል ጠበቆቹ አስረድተዋል፡፡

የወንጀል ሕግ 67 ቢሆንም ዋስትና አክብሮ አይቀርብም የሚለውን ስለሆነ፣ ዋስትና የሚፈቀደው መልክ ታይቶ፣ አቅም ታይቶ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ፣ መቃወሚያው ትክክል አለመሆኑን ጠበቆቹ ተቃወሙዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ መብት ሲያስከብር አቅም ያለው፣ የሌለው ስለማይል ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የሚቀርቡትን ሌሎች አማራጮች ሊያይ እንደሚገባም ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን መቃወሚያ ውድቅ አድርጐ ደንበኛቸውን በዋስ እንዲለቀው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ወገን አዳምጦ ዓቃቤ ሕግ በወንጀል ሕግ 63 መሠረት ያቀረበውን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ፣ በወንጀል ሕግ 67 ላይ በተጠቀሰው መሠረት ሲታይ ወንጀሉ ከባድ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ቢለቀቅ ይቀርባል የሚል እምነት ስለሌለው፣ የዋስትና መብቱን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን በመግለጽና ማረሚያ ቤት እንዲቆይ በማዘዝ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

ምንጭ ሪፖርተር

Latest Posts

 


 

 

 

 

 

Advertisements

What do you say about this? እርስዎ ምን ይላሉ?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s