Uncategorized

ከኮንዶምንየም ምዝገባው ሰልፍ መሀል

addis-street_5819

‘አይ መድሃኔአለም፡፡ አንተ ምን አለብህ እንዲህ የተንጣለለ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለህ’

“ስቴዲየሙን ነው የምፈልገው እኔ”  ስቱዲዮ ማለታቸው ነበር፡

ግንቦት 27/2005 ወደ ስራዬ ከመግባቴ በፊት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦሌ መድሃኔአለም ቅርንጫፍ ሄድኩ፡፡ አዲሱን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ዝግ የባንክ ሂሳብ ለመክፈት በቤት ጉዳይ የተማረሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎችን ማልደው ደጅ እየጠኑ ነው፡፡ እኔም ተቀላቀልኳቸው፡፡ ከሰልፈኞቹ መሀል በተስፋ፣ በጥርጣሬና በጉጉት የተሞሉ ቃላት ይሰነዘራሉ፡፡  “አይ   ደሃ መቼም ጉጉ ነው” ይላሉ አንዱ መቼም አይደርሰኝም፤ እስኪ ለማንኛውም ልሞክረውና ሰው የሆነውን እሆናለሁ የሚል አይነት ስሜት ያላቸው አዛውንት፡፡ “አሁን ሰባት አመት ጠብቀንስ ይደርሰን ይሆን” ቀጠሉ ፡፡ ሰውየው በእድሜ የገፉ ከመሆናቸው የተነሳ ቢያንስ የህይወታቸውን የመጨረሻ ጎዜያት በራሳቸው ቤት አረፍ ብለው የማሳለፍ ትልቅ ምኞት እንዳላቸው መገመት አይከብድም፡፡

“እንዳው አንተ መድሃኔአለም እኔንም ከሰው እኩል ታደርገኝ ይሆን፡፡” አሉ ከኋላዬ የቆሙ አንዲት እድሜያቸው 50ዎቹ ውስጥ የሚገመት እናት ወርሃዊ በዓሉ እየተከበረ ወዳለው ወደቦሌው መድሃኔአለም ፊታቸውን አዙረው፡፡ ሴትየዋ ነጫጭ በለበሱ ምዕመናን የደመቀውን ቤተክርስቲያን በአርምሞ ይመለከቱታል፡፡ ‘አይ መድሃኔአለም፡፡ አንተ ምን አለብህ እንዲህ የተንጣለለ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለህ’ የሚሉ ይመስላሉ እጆቻቸውን አፋቸው ላይ አድርገው ቤተክርስቲያኑን የሚያዩበት ሁኔታ፡፡ “አደራህን” አሉ ሴትየዋ ከዝምታ ቆይታቸው በኋላ ፊታቸውን  የባንኩ በር የሚከፈትበትን ሰዓት ወደሚጠብቁት ሰልፈኞች እየመለሱ፡፡ እጃቸው ላይ ያለውን ፎርም እያገላበጡ ያዩታል፡፡ ሰልፈኞቹ እስክርቢቶ እየተዋዋሱ ፎርሙን መሙላት ተያይዘውታል፡፡ ይሄን ጊዜ አዛውንቷ ከፊታቸው ያለውን ወጣት “እባክህ የኔ ልጅ የኔንም ሙላልኝ፡፡” ብለው ፎርሙን አቀበሉት፡፡

ልጁ ፎርሙን መሙላት ጀመረ፡፡ “ባለስንት ነው የሚመዘገቡት እማማ?” ባለስንት መኝታ ቤት ማለቱ ነው፡፡

“ስቴዲየሙን ነው የምፈልገው እኔ”  ስቱዲዮ ማለታቸው ነበር፡፡ ልጁ በአነጋገራቸው ፈገግ ብሎ የ10/90ው ቦታ ላይ ምልክት አድርጎላቸው ቀጠለ፡፡ ፎርሙ ላይ በቅድሚያ የሚያስቀምጡት ገንዘብ የሚለው ጋር ሲደርስ ድጋሚ ጠየቀ፡፡ “ስንት ብር ነው አሁን የሚያስቀምጡት” ሴትየዋ ግራ በመጋባት ዝም ብለው ሲያዩት ለመነሻ የሚሆነውን የመጀመሪያ ወር ቁጠባ 187 ብር ሞላው፡፡ እጃቸው ላይ ጭብጥ አድርገው የያዟትን ቦርሳ መታዊያቸውን ኮፒ ሊያስደርጉ ሲከፍቱ አትኩሬ አየኋት፡፡ 190 ብር ይዘዋል፡፡ ምናልባትም ያላቸው ቀሪ ሂሳብ 3 ብር ብቻ፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ የባንኩ በር የሚከፈትበት ሰዓት ደረሰ፡፡ ሰልፈኞቹ ወደ ውስጥ ዘለቁ፡፡ ባንኩ ግን ጉዳያቸውን ለመፈፀም  ማልደው ከቤታቸው የወጡትን ሰዎች ለማስተናገድ ዝግጁ አልነበረም፡፡  የባንኩ ሰራተኞች የባንኩ ሲስተም እንደማይሰራ ገልፀው ፎርሙን ከመታወቂያ ኮፒና ከሁለት ጉርድ ፎቶ ግራፎች ጋር እየሰበሰቡ አስቀመጡት፡፡

ሰልፈኞቹ  “እዚሁ እንጠብቅ?”

ባንኩ “አይ አሁን መሄድ ትችላላችሁ”

“በኋላ እንመለስ?”

“ትናንትናም ከእናንተ በፊት መጥተው የተመለሱ ሰዎች አሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ሂዱ፤ ሲስተሙ ሲሰራ እንደውላለን”

እኔም ከሰልፈኞቹ ነጠል ብዬ ጠየቅኩ፡፡  “የንግድ ባንክ ሲስተም የሚሰራው ግን መቼ መቼ ነው?”

መልስ ግን አላገኘሁም፡፡ ጥያቄውን የጠየቅኩት ለእራሴ ነዋ፡፡

በፍቃዱ በየነ

Advertisements

One thought on “ከኮንዶምንየም ምዝገባው ሰልፍ መሀል

What do you say about this? እርስዎ ምን ይላሉ?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s