Uncategorized

የሴቶች 5000 ፍፃሜን እኔ እንዳየሁት እናንተ አትዩት

Meseret-Defar
የሞስኮውን አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወንዶች ማራቶን ፍፃሜ ባለማየቴ የተፈጠረብኝ ቁጭት፣ ብስጭትና በሰውነቴ ውስጥ ያለው የንዴት ስርጭት እንደቀጠለ ነው፡፡ ትክን ያሉት ጨጓራዬ፣ አንጀቴና ቆሽቴ የተሰማቸውን ስሜት በሰላማዊ ሰልፍ እየገለፁ ነው፡፡ ድርጊቱንም በፅኑ አውግዘዋል፡፡

እንደ መብረቅ ብልጭ እያለ ሲጠፋ የዋለው መብራት የሴቶች አምስት ሺህ ሜትር ፍፃሜ ውድድር ሊጀመር ግማሽ ሰዓት ሲቀረው መጣ፡፡ “ጎሽ! ምና አለ ይሄን ውድድር አይቼ ከፈለገ እስከወዲያኛው ቢጠፋ” አልኩ በተደበላላቀ ስሜት፡፡

እሱ ምን በወጣው እቴ፡፡ ልክ ቦታ ቦታቸውን ከያዙት አትሌቶች መካከል የካሜራውን አይን እየተከተልኩ መሲን ሳማትር ድርግም!

“እውነት! በቃ እንደዚህ መጨካከን ተጀመረ?” ጠበኩት የለም… ጠበኩት የለም:: ለረዣዥም 120 ሰከንዶች ጠበኩት፤ እሱ እቴ፡፡ ጃኬቴን እየለበስኩ ወደ አምፖሉ አንጋጠጥኩ፡፡ ለሚያየኝ ሰው የኤሌክትሪክ መና ከሰማይ የምጠብቅ ነው የምመስለው፡፡ አሁንም አልመጣም፡፡

የቤቴን በር ቆልፌ ከመውጣቴ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ አንገቴን ሰገግ አድርጌ አየሁት፤ አይመጣም፡፡ ቢያንስ ይሄኛው ሩጫ ፈፅሞ ሊያመልጠኝ አይገባም፡፡ ግን ምን ያደርጋል፡፡ ከአሁን በኋላ ከቤቴ ብወጣስ መሲ በፈጣን እግሮቿ 5000 ሜትሩን ፉት ሳታደርገው የት መድረስ እችላለሁ፡፡

ከግቢ ስወጣ የተከራየሁበትን ቤት ግቢ በር ጓ አድርጌ ዘጋሁት፡፡ ( ሆ… ሆይ! ጥጋበኛ ተከራይ ንዴቱን በግቢው መዝጊያ ይወጣል አሉ)

ውስጤ ያለው የጉጉት ስሜት ከተስፋ መቁረጥ ጋር ተደማምሮ እግሮቼን አስሯቸዋል፡፡ በዝግታ በመራመድ ላይ ነኝ፡፡ የአስፓልቱን ጥግ ይዤ ላይ ታች እያልኩ ስንጎራደድ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡ ከሰፈራችን ራቅ ብሎ የሚገኝ አንድ አትክልት ቤት በቅርቡ ጀነሬተር ገጥሟል፡፡

ምን ዋጋ አለው፡፡ በእርግጠኝነት ውድድሩ ተጀምሯል፡፡ ጓደኛዬ ጋር ስልክ ደወልኩ፡፡
“ተጀመረ?”
“ አራት ዙር” አለችኝ
“የሮጡት ነው የቀራቸው?” እኔም ውድድሩ ሳያልቅ ጀነሬተሩ ካለበት ለመድረስ የቀረኝን ጊዜ እያሰብኩ ነበር፡፡
“እ” አለችኝ ያልኩት ስላልተሰማት፡፡
“አራት ዙር፤ የሮጡት ነው የቀራቸው?”
“እ” አለችኝ አሁንም፡፡ መደማመጥ አልቻልንም፡፡
“ኢ አትበይ” አልኳት፡፡ ደግነቱ አልሰማኝም፡፡
ስልኩ ተቋረጠ፡፡ ኔትወርክ፡፡

መልሼ ደወልኩ፡፡ “መስመሮች ሁሉ ለጊዜው ተይዘዋል”፡፡ ኧረ እባክሽ ኤጅ ኤጅ ኤጅ ኤጅ ኤጅ… አንድም ሳይቀር?!  “አባክዎን ትን….” የጀመረችውን ሳትጨርሰው ጆሮዋ ላይ ዘጋሁባት፡፡

ከራሴ ጋር ግብግብ …

“መስመሮቹ ግን የተያዙት እውነት ለጊዜው ነው ወይስ በሊዝ? ቆይ ኔትወርክም ‘ኤክስፖርት’ ማድረግ ጀመርን እንዴ?

እየውላችሁ ያልሆነ ነገር ስናገር፡፡ ምናለበት አሁን በቅንነት ባየው፡፡ ምናልባት እኮ ይሄኔ ኢትዮጵያዊ ሁላ ከሀገር ውስጥም ከውጪም እየተደዋወለ መሲ ሪከርድ ትሰብራለች አትሰብርም የሚል ውርርድ ገጥሞ ይሆናል፡፡ በቃ ቁማሩ ሲያልቅ መስመሮች ሁሉ ይለቀቁልሃል፡፡ አቦ ተረጋጋ!”

እስካሁን ካባከንኩት ጊዜ አንፃር በቃ አሁን ውድድሩ ሊጠናቀቅ ግፋ ቢል አራት ዙር ቢቀረው ነው፡፡ ከመጠናቀቁ በፊት ጄነሬተሩ ካለበት ጭማቂ ቤት እንደማልደርስ አውቄዋለሁ፡፡ ያም ሆኖ የሆነ ውስጣዊ ኃይል እግሮቼን ያወናጭፋቸው ገባ፡፡ መሲ እዛ ወደ ወርቁ በፍጥነት ትምዘገዘጋለች እኔ እዚህ አሷን ለማየት ቁልቁል እንደረደራለሁ፤ ወደ ጀነሬተሩ ፡፡

ምንም እንኳን ህይወት ራሷ በሩጫ የተሞላች ቢሆንም የእንዲህ አይነቱ ሩጫ ልምድ የለኝም፡፡ ዛሬ ግን የግድ ሆኖብኝ እሮጣለሁ፡፡ የአሌክትሪክ ኃይል ፍለጋ፡፡ ሰፈራችን ካለው እንጨት መሸጫ አካባቢ ስደርስ አንድ ጎልማሳ ሰውዬ እና አንድ ወጣት ጆሮዎቻቸውን ገጥመው እንጨት ላይ ቁጭ ብለዋል፡፡ መሃል ላይ አንድ ስልክ አለች፤ የቻይና፡፡

ሩጫውን በሬዲዮ እየተከታተሉ እንደሆነ እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ እነሱም መብራት ጠፍቶብኝ ፍለጋ እንደወጣሁ እርግጠኛ ሆነዋል፡፡ “ና ና እዚህ፡፡ ሊያልቅ ነው” አለኝ ወጣቱ፡፡ ተቀላቀልኳቸው፡፡ እኔም ጠጋ ብዬ ጆሮዮን ቀሰርኩ፡፡

ቁጭ ብዬ ትንፋሼን እንኳን ሳልሰበስብ የመጨረሻው ዙር ደወል ተደወለ፡፡ “ኦ ያ ያ! ኦ ያ ያ! ኦ ያ ያ!”

በነገራችን ላይ ማንኛውንም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በሬዲዮ መከታተልም ሆነ “ማየት” ማለት መበደል እንደሆነ የገባኝ ዛሬ ነው፡፡ ምንድ ነው “ኦ ያ ያ! ኦ ያ ያ! ኦ ያ ያ!”  ከ ኦ ያ ያ ባዩ የስሜት ሙቀትና ከፍታ ውጪ ምንም ትርጉም የማይሰጥ፤ ምን እየተከናወነ እንደሆነ በእርግጠኝነት ለመገመት የሚያዳግት አንድ አይነት ጩኸት፡፡ ኮሜንታተር ዱሮ ቀረ፡፡ በእነ ደምሴ ዳምጤ ጊዜ፡፡

መሲ የመጨረሻውን መስመር ካለፈች ከረጅም ጩኸት በኋላ እንዳሸነፈች አወቅን፡፡ መብራት ጠፍቶ ያገናኘን ሶስት ኢትዮጵያውያንም በደስታ እየጮኽን ተቃቀፍን፡፡ እሰይ አንጀቴ ቅቤ ጠጣ፡፡ ንዴቴም ቀዘቀዘ፡፡

ቀጥሎ ያለውን ነገር ለመስማት አልቻልንም ነበር፡፡ ቻይናዊቷ ሞባይል ባትሪ ጨርሳ ዘግታለች፡፡“ዱሮስ የቻይና ሞባይልና ኔትወርክ” ልል አሰብኩና “ለነገሩ አልፈርድባትም ዛሬ ቀኑን ሙሉ ኤሌትሪክ አላገኘችም” ብየ ተውኩት፡፡

ወደ ቤቴ ስመለስ “ኤጭ ወይ ገጠር አይሉት ከተማ” ይላሉ አከራዬ እትዬ ጥሩዬ፡፡ እሳቸውም እንደኔ በመብራት መጥፋት ምክንያት ሩጫውን ባለማየታቸው ተበሳጭተው ኖሯል፡፡ ከግቢ ስወጣ በኃይል የዘጋሁትን በር ከፍቼ ስገባ ምንም አላሉኝም፡፡ ተሯሩጬ ይዤው የመጣሁት “ኢትዮጵያ አሸነፈች” ዜና አስረስቷቸዋል ማለት ነው፡፡

“ውድድሩ እጅግ ያምር ነበር፡፡ በተለይ የመሰረት አጨራረስ ምናምን” እያልኩ ልተርክላቸው አልፈለግኩም፡፡ መዋሸት ጥሩ አይደለም፡፡ ሩጫውን ለማየት ከቤቴ ወጥቼ ስሮጥ መንገድ ላይ ቁጭ ብለው ሬዲዮ ከሚያዳምጡ ሰዎች ጋር ተለጠፍኩ፡፡ ቁጭ እንዳልኩ መሰረት አሸነፈች፡፡ በቃ፡፡ ሌላውን አላየሁም አልሰማሁምም፡፡

ወደ ቤቴ ስገባ ጭለማ ውጧታል፡፡ በቅርቡ በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ እያለሁ የፃፍኳቸው ስንኞች መልሰው በህሊናዬ አንቃጨሉ

መብራት የተሳነው
ትንሿን ጎጆዬን ብርሃን ናፍቋታል
ግና “መብራታችን”
አለመብራት እንጂ መብራት ተስኖታል
መጥፋቱንስ ደግ ነው መብራት ግን ጠፍቶታል

ሻማ አብርቼ ብዕሬን አነሳሁ፡፡ እንደዚህም ፃፍኩ፡፡ ተነፈስኩም………በከፊል፡፡

ማሳረጊያ አንቀፆች

ይሄን ፅሁፍ ጦማሬ ላይ ለማስፈር የጭን ገረዴ (Laptop) ታስፈልገኛለች፡፡ ስጠብቅ አመሸሁ፤ መብራቱን፡፡

ቀን ለአፍታ ብልጭ ባለበት ቅፅበት ብረት ድስቴን በጥድፊያ ጣድ አድርጌ ማቁላላት የጀመርኩት ሽንኩርት ለወግ ማዕረግ መድረስ አልቻለም፡፡ አይደለም ለምሳና ለመክሰስ፤ ለእራት እንኳን፡፡ የኤሌክትሪክ ምድጃ ገዛሁ ብዬ ቡታጋዜን የጣልኩባትን ቀን ረገምኩ፡፡ “ወግ እንቅ” አለች አያቴ፡፡

ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ እንደገና ብልጭ ብሎ ጠፋ፡፡ በቃ ይሄ “መሼ ደህና እደሩ” ወይም “አልመጣም ቀረሁኝ” ማለት ነው ብዬ አንሶላዬ ውስጥ ተከተትኩ፡፡

(በፍቃዱ በየነ)

Advertisements

4 thoughts on “የሴቶች 5000 ፍፃሜን እኔ እንዳየሁት እናንተ አትዩት

  1. Pingback: ስንት ሰው ባዶ እግሩን በሚዳክርባት ሀገር ስለ ሩኒ ጫማ አውልቆ በካልሲ መሄድ ማውራት ስድብ አይደለምን | Ethiopianobserver

  2. Pingback: ስንት ሰው ባዶ እግሩን በሚዳክርባት ሀገር ስለ ሩኒ ጫማ አውልቆ በካልሲ መሄድ ማውራት ስድብ አይደለምን | Ethiopianobserver

  3. Pingback: ሀይቅን ለእነ ባህር ዳር ብቻ ማን ሰጣቸው? አዲስ አበባም ሀይቅ አላት | Ethiopianobserver

What do you say about this? እርስዎ ምን ይላሉ?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s