East Africa

Eritrean army burned a school and bus in Badime /የኤርትራ ጦር በባድመ አንድ ትምህርት ቤትና አንድ አውቶብስ አቃጠለ

የኤርትራ ጦር በባድመ አንድ ትምህርት ቤትና አንድ አውቶብስ አቃጠለ የኢትዮጵያ ሠራዊት በቅርቡ በባድመ ግንባር የኤርትራ ግዛት ውስጥ በመግባት በሦስት ወታደራዊ ካምፖች ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ፣ የኤርትራ ጦር በባድመ ውስጥ የሚገኘውን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና አንድ አውቶብስ ማቃጠሉን ምንጮች ጠቆሙ፡፡

የአካባቢው የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ባለፈው እሑድ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በባድመ ግንባር የሚገኘው የኤርትራ ጦር ኃይል በከባድ መሣርያ (ተወንጫፊ) ባደረሰው ጥቃት፣ ‹‹ባድመ ቀዳማይ ብርኪ ቤት ትምህርቲ›› (ባድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት) ሙሉ ለሙሉ በመቃጠሉ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ ትናንት ደግሞ በከተማዋ ውስጥ ቆሞ በነበረ አንድ አውቶብስ ላይ በተመሳሳይ በደረሰው ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ተቃጥሏል፡፡

በሁለቱም ጥቃቶች በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኤርትራ የነፃነት በዓል በማክበር ላይ ሳለች ድንበር ጥሶ በመግባት በባድመ ግንባር በሚገኝ አንድ ብርጌድ ላይ ጥቃት ያደረሰው፣ ከዚያ ቀደም ሲል የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት በባህላዊ መንገድ የወርቅ ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን በተደጋጋሚ እያፈነ በመውሰዱ ምክንያት ነው፡፡

ባለፈው ዓመት በኤርትራ ላይ ያለውን ፖሊሲ ‹‹ከመከላከል ወደ ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰድ›› የለወጠው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በአፋር አካባቢ በኢትዮጵያውያንና በአውሮፓውያን ቱሪስቶች ላይ ከኤርትራ በኩል ጥቃት በመሰንዘሩ አፀፋ ወታደራዊ ዕርምጃ መውሰዱ የሚታወስ ነው፡፡

ምንጭ ሪፖርተር

What do you say about this? እርስዎ ምን ይላሉ?